ዲዚኛ English አማርኛ
Diizi and Diizi Area Scholars

የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ

August 30, 2025 1.2K Views 5 min read National Park Maji
የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ

ይህ የኦሞ ብሄራዊ ፓርክ በሃገራችን ውስጥ ከሚገኙ እድሜ ጠገብት ፓርኮች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ሲሆን ፓርኩ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጡ ዙሪያው በተለያዩ ማህበረሰቦች የተከበበ በመሆኑ ከ1900 ዓ.ም ጀምሮ በዙሪያው ባሉ ማህበረሰቦች በአደን እና በመሳሰሉ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲጠቃ የኖረ ነው፡፡የፓርኩ ዙሪያ በአብዛኛው በዲዚ፤የተወሰነው በደቡብ ምስራቅ ኦሞ ወንዝ ዳርቻ ላይ በሙርሲ፤እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ የኪቢሽ ወንዝን ተከትሎ እስከ ደቡብ ሱዳን ጫፍ ድረስ በሱርማ ማህበረሰብ ነዋሪዎች የተከበበ ነው፡፡

የኦሞ ብሄራዊ ፓርክ የ5141 ስ.ኪ.ሜ ስፋት ሲኖረው በውስጡም በርካታ ውድና ብርቅዬ የዱር እንስሳትን አስጠልሏል፡፡ለዚህም እንደምሳሌ ዝሆን፣አንበሳ፣አቦሸማኔ፣ጎሽ፣ቀጭኔ፣ውድንቢ፣አውራሪስ፣ቀበሮ እና የመሳሰሉትን ሌሎችም በርካታ የእንስሳት ዝርያ የያዘ ሲሆን ከመዲናችን አ.አ በ867ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ፓርኩ ከ1900ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ አደንና መሰል ድርጊቶች ሲጠቃ የዘለቀ ቢሆንም በህጋዊ መንገድ በፓርክነት ተከልሎ አገልግሎት መስጠት የጅመረው ግን በ1967 ዓ.ም ነው፡፡

ይህ ውድንቢ(ግዙፉ የአፍሪካ አጋዘን አስተኔ) በመባል የሚታወቅ ሲሆን በሃገራችን ኢትዮጵያ በኦሞ ብሄራዊ ፓርክ ብቻ ተወስኖ የሚገኝ እንስሳ ነው፡፡ እንዲሁም ከሃገራችን ውጭ በደቡብ ሱዳን፤በደቡብ ሱማሌ፤በኬኒያና በታንዛንያ ይገኛል፡፡

ይህ ውድንቢ ወይም ግዙፉ የአፍሪካ አጋዘን አስተኔ ወንዱ በአማካይ ከ500 እስከ 600ኪ.ግ ሴቷ ደግሞ ከ340 እስከ 445ኪግ ይመዝናሉ፡፡ቁመታቸውም እስከ 180 ሴንቲ ሜትር የሚረዝም ሲሆን ከከፊል በርሃማ እስከ ተራራማ ስፍራዎች ተሰራጭተው ይኖራሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አንጋፋው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ

ከ75 በላይ አጥቢ እንስሳት

ከ325በላይ የተለያዩ ማራኪ የአእዋፍ ዝርያዎች
ከ600 በላይ የእጽዋት ዝርያዎች

ከ24 በላይ የእባብና እንቁራሪት ዝርያዎች

ከ13በላይ የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎችን እና ሌሎችም በርካታ የዱርና የተፈጥሮ ፀጋዎችን የታደለና የተሸከመ የተፈጥሮ ሃብታም ፓርክ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ ይህ የኦሞ ፓርክ በበርካታ ሰው ሰራሽ ችግሮች የታጠረና በርካታ ስጋቶች የተጋረጡበት ፓርክ ነው፡፡ቀደም ሲል እነደገለፅነው ለዘመናት በአደን እና መሰል ችግሮች የተጋለጠ ፓርክ ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ ደግሞ በወቅታዊነት በአቅራቢያው ግዙፉ የስኳር ፋብሪካ መገንባት ደግሞ ሌላኛውና ወቅታዊው አንገብጋቢ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የህልውናው ስጋት ነው፡፡

National Park Share:
Back to All Maji Tourism